የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች (ክፍል ፩)
አብዛኞቹ የሃገራችን ኢንዳስትሪዎች ለአቅርቦት
ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና ብዙም ትኩረት ሲሰጡ አይታይም፡፡ የብዙዎቹ ኢንዳስትሪዎች ትኩረትም አምርተው በሚሸጡት ምርት
ዓይነትና ብዛት እንዲሁም የውስጥ አቅምን ማሳደግ ላይ እንጅ በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ባላቸው ጥምረት (የቅንጅት ሥራ) ውጤት
ላይ አይደለም፡፡አስቀድሞም በቅድመ ትግበራና የአዋጭነት ጥናት ወቅትም ቢሆን ለአቅርቦት ሰንሰለት ትኩረት ስለሚነፈገው አዲስ
የሚከፈቱ ኢንዱስትሪዎች ከየት ጥሬ ዕቃ እንደሚያገኙ፣ ከማን ጋር
አብረው መስራትና እንዴት መስራት እንዳለባቸው ሳይጤን ዘለው ወደ የማምረቻ ፋብሪካ (የአገልግሎት መስጫ ተቋም) መክፈት መሄድ
የሚታየው፡፡
በዚህ ዘመን እንደሚታየው ደግሞ የገበያ ፉክክሩ
የአንድ አምራች/አቅራቢ/ ድርጅት ከሌላ ተመሳሳይ ምርት አምራች/አቅራቢ/ ድርጅት ጋር ሳይሆን የአንድ ምርት የአቅርቦት
ሰንሰለት ከሌላ ተመሳሳይ የአቅርቦት ሰንሰለት ጋር ያለ ፉክክር ነው፡፡ በዚህ የፉክክር ገበያ ውስጥ አሸናፊ ለመሆን የአቅርቦት
ሰንሰለትን መሰረት በማድረግ መቀናጀት ያስፈልጋል፡፡ የተናጠል ሩጫ የትም ስለማያደርስ በተለይም ገና ላላደጉ ኢንዳስትሪዎቻችን
እርስ በርስ በመቀናጀትና በመመጋገብ መጓዝ ካልተቻለ አገር አቀፋዊ ሆነ አለም አቀፋዊ ብቁ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም፡፡
ውድድሩ የአቅርቦት ሰንሰለት እንጅ የተናጠል ውድድር አይደለምና፡፡የአቅርቦት ሰንሰለት ጥምረት ዋና ዓላማም የደንበኛን
ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ በማርካት ከሌላው የአቅርቦት ሰንሰለት ልቆ በመገኘት በገበያ ላይ የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን ነው፡፡ጥምረቱ
በመረጃ መቀናጀትን፣የእቅድ ጥምረትንና የአሠራር ሂደት ጥምረትን ያካትታል፡፡
በአብዛኛው የኢንዱስትሪዎቻችን የስራ ባህልም “የቀጥታ ግልበጣ” ን ወይም “የኩረጃን” ልምድ መሠረት ያደረገና ተመሳሳይ
አሠራርን የተከተለ ነው፡፡ ይህም ማለት በአንዱ ፋብሪካ የታየው አሠራር ምንም ጥቅምና ጉዳትን የማገናዘብና የማስላት ስራ
ሳይካሄድበት በተመሳሳይ ወቅትና ሁኔታ ተደጋግሞ ሲሰራበት ይታያል፡፡ ካደጉ አገሮችም ሆነ ከተፎካካሪ ሃገር በቀል ኢንዱስትሪዎች
ኮርጆ እሴት ጨምሮ መወዳደር ጤናማና አዋጭ ስለሆነ እንደርሱ አይነቱ ኩረጃ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ በአለም ላይ ያለውም ልምድ
የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የቻይና
ኢንዱስትሪዎችን ብንወስድ በአብዛኛው በመኮረጅ፣ በማላመድና በማሻሻል ላይ ያተኮረ ስልት ይከተላሉ፡፡ ኮርጀው ካገኙት ላይም እሴት በመጨመርና በማሻሻል የተሻለ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ነገር ግን በእኛ
ሃገር ኢንዱስትሪዎች (ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ባሉ
ኢንዱስትሪዎች) ዘንድ የሚታየው አዋጭነትንና አቅምን እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫን ሳያገናዝቡ ወደ ጭፍን ኩረጃ የሚሄዱና
በመጨረሻም የማይሳካላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡
አንዱ ኢንዱስትሪ ከሌላው ጋር ተባብሮ የመስራት ባህልም የዳበረ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ዘርፍ በተለይ የለም ቢባል ይበልጥ
ያስማማል፡፡ በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ በተመጋጋቢነትና
በመቀናጀት ከመስራት ይልቅ በተናጠል መስራት የጎላ ባህላችን ነው፡፡ ይህ ባህል ይበልጥ ጎልቶ የሚንፀባረቀውም ከሀገራዊ/ከሃገር
በቀል/ ኢንዳስትሪዎች ጋር አብሮ ከመስራት (ከመመጋገብ) ይልቅ ከሌሎች ኢንዳስትሪዎች ጋር “የማያዛልቅ”ና የማያዋጣ ጥምረት
ሲፈጠር ይታያል፡፡ ማንም ኢንዱስትሪ ከሚፈልገው ጋር መተሳሰርና መመጋገብ የራሱ ምርጫ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በይበልጥ
አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ካለው መሰል ሃገራዊ/ሃገር በቀል/
ኢንዱስትሪ ጋር ተቀራርቦና ተመጋግቦ መስራቱ ይበልጥ ጠቃሚ ነው፡፡ የሃገሪቱም ኢንዳስትሪዎች እርስ በርስ ተመጋግበው ያለመስራታቸው ጠንካራና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ
እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋልና፡፡
ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment