Tuesday, September 10, 2013

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት ተቋቋመ (የእሑድ እትም ጳጉሜን 3 ቀን 2005 Reporter)

ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኩባንያዎችን ለመደገፍ ‹‹ብሔራዊ የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት››
በሚባል መጠሪያ የተቋቋመውን ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይመሩታል::
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባፀደቀው ደንብ መሠረት የተቋቋመው ይህ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ
ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ኩባንያዎችን የሚደግፉ መመርያዎችን ከማውጣት ባሻገር፣ ኩባንያዎች ያሉባቸውን
ችግሮች በመፍታት በኩል ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል:: ቀደም ሲል ብሔራዊ የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ
የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎችን ሲደግፍና ሲያበረታታ እንደነበር የሚታወስ ነው::
ይህንን የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ ወደ ምክር ቤት ደረጃ ማሳደግ ያስፈለገው፣ ኩባንያዎቹ የሚሰጣቸውን
ድጋፎች ለማብዛትና የምክር ቤቱን ተሳታፊዎች ከፍ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው
ለሪፖርተር ገልጸዋል::
በዚህ መነሻነት ቀደም ሲል የነበረው ብሔራዊ የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ በመንግሥት ኤጀንሲዎች
ታጥሮ የነበረ በመሆኑ፣ በአዲሱ ምክር ቤት ውስጥ በወጪ ንግድ ተሳታፊ የሆኑ የግሉ ዘርፍ አባላትን እንደሚያቅፍ
ተነግሯል::
‹‹ምክር ቤቱ የሚመለከታቸው ጉዳዮች እንዲበዙ ከመደረጉም በተጨማሪ፣ የኤክስፖርት ዘርፍ አፈጻጸምን
በቅርበት ይከታተላል፤›› ሲሉ አቶ አህመድ አክለው ገልጸዋል:: ኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም. ባፀደቀችው የዕድገትና
ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመምራት ላይ የሚገኘው የግብርና ዘርፍም ሆነ፣ የዕቅዱ ዘመን ማብቂያ
ከሆነው 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ኢኮኖሚውን የመምራቱን ተግባር ከግብርና ይረከባል ከተባለው ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ
ብዙ ይጠበቃል::
በ2006 ዓ.ም. የበጀት ዓመት መንግሥት በአጠቃላይ ከኤክስፖርት ዘርፍ 5.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዷል::
ከዚህ ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንደሚገኝ ሲታቀድ፣ የተቀረውን ከማዕድን፣ ሆርቲካልቸርን
ጨምሮ ከግብርናው ዘርፎች እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጓል:: ምንጮች እንደገለጹት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር
ኃይለ ማርያም ይመራ የነበረው የቀድሞ ብሔራዊ የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ ከአንድ ወር በፊት ከሁሉም ዘርፎች በ2006
ዓ.ም. ይገኛል በተባለው ገቢ ባለመርካቱ ዕቅዱ በድጋሚ ተለጥጦ እንዲቀርብለት አዟል::
ቀደም ሲል በአጠቃላይ የቀረበለት የኤክስፖርት ገቢ ምጣኔ ከ4.5 ቢሊዮን ብር የማይበልጥ ነበር:: ተለጥጦ ይቅረብ ተብሎ
ከተወሰነ በኋላ ሁሉም የኤክስፖርት ዘርፎች በድጋሚ ያሏቸውን አማራጮች እየገመገሙ የገቢ ዕቅዳቸውን ከፍ ማድረጋቸው ተመልክቷል::
በ2005 ዓ.ም. ከኤክስፖርት ይገኛል ተብሎ የታቀደው አምስት ቢሊዮን ዶላር የነበረ ቢሆንም፣ በተጨባጭ የተገኘው ግን 3.08 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው::
ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተገኘው ደግሞ ከተጠበቀው በታች 300 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት ከዚህ ቁጥር እጅግም ከፍ ያላለ ገቢ እንደሚገኝ ነበር የታቀደው:: አቶ አህመድ የቀረበው የኤክስፖርት ገቢ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ከማሳካት
አንፃር ያነሰ ነበር ብለው፣ በድጋሚ ከተከለሰ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የዕቅዱን 80 በመቶ ለማሳካትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ በሚታቀደው ዕቅድ ላይ 20 በመቶ ተጨማሪ ተደርጎ ይታቀዳል ብለዋል:: በዚህም የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ጨምረው ገልጸዋል:: አቶ አህመድ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ በአሁኑ ጊዜ ኩባንያዎች ከአቅማቸው በታች የሚያመርቱና ምርታማነታቸውና ከመንግሥት የሚሰጣቸው ድጋፍም አነስተኛ መሆኑ በግምገማ የተደረሰባቸው ነጥቦች መሆናቸውን ገልጸው፣ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ቀጣይ ሥራ እንደሚሠራ ታሳቢ በማድረግ የቀድሞ ዕቅድ ተከልሶ እንዲቀርቡ መደረጉን አስረድተዋል::

Wednesday, June 19, 2013

በእንተ METEC

METEC (Metal and Engineering Corporation- ብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን) እንደ ሀገር አቀፍ ኮርፖሬሽን ትኩረት ሰጥቶ በተወሰነ የኢንዳስትሪ ዘርፍ ላይ ሊሰራው የሚችል ብዙ ነገር አለ። እየሰራም አሳይቷልና። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ግን ሁሉን ልያዘው ማለቱ ካስደሳችነቱ ይልቅ አሳሳቢነቱ ያይላል(ወታደር የማይችለው ነገር የለም ብለን ካላለፍንው በቀር)።
የግሉን ኢንዳስትሪ ዘርፍ በማሳደግ ማደግ የሚል ፖሊሲ ያለው መንግስት ኮርፖሬሽን አቁቁሞ ከዝናብ ልብስ እስከ ብርድልብስ ፣ ከሺቦ እስከ ትራንስፎርመር ፣ ከፕላስቲክ እስከ ፀሐይ ፓኔል፣ ከታንክ እስከ ድሮን ፣ከማዳበርያ እስከ ስካር.....ከ እስከ ከ ያለዉን ሁሉ እኔ ልያዘው ፣ ላምርት ልሽጠው ካለ ወይ ፖሊሲው ይቀየር ወይ አተገባበሩ ይስተካከል ያስብላል። ግለሰብና መንግስት ተመካክረው ተደጋግፈው ያድጋሉ እንጅ አይፎካከሩም። እኩል ሜዳ በሌለበት ሊፎካከሩ ቢያስቡም የማይጣጣም ፉክክር ይፈጠራል፣ ድል ተነሺም በጧት ይታወቃል። ነሐሴ ላይ የጥናት መረጃ ስሰበስብ በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጅ ዙሪያ በግልም በሽርክናም ስራ ሊጀምሩ ተዘጋጅተናል ያሉኝ የግል ኩባንያዎች የካቲት ላይ ቅዝቅዝ ብለው ነው ያገኘሁዋቸው (ቅዝቃዜው ደግሞ የMETECን አንድም ሀገር በቀል የግል ኩባንያ ሳይዝ ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር በጥምረት የጀመረዉን የሶላር ፓኔል ማምረት ስራ ተከትሎ መሆኑ ነው። )

METEC ባሁኑ ሰዓት 16 "ኢንዳስትሪዎችን" ያስተዳድራል። ባንዱ እንዳስትሪ ስር ከሰባት እስከ ስምንት የሚደርሱ ፋብሪካዎችን ይይዛል።
ለምሳሌ:- በEthiopia Power Engineering Industry ስር የተካተቱት
 1.Transformer Production Factory(upto 1250KVA rating)
 2. Wire & Cable production Factory
3.Automatic Power factor corrector & Compact substation production Factory
4. Motor & Generator Production factory
5.Engine Production Factory (including heavy duty )
6. Turbine Production Factory እና
7. Solar Panel Production Factory (upto 30MW/yr) ናቸው።

ይሄን ሁሉ እያስተዳደሩ ያሉት ደግሞ ትናንት ሀገር ጠብቁልን ያልናቸው መከላከያ ሠራዊት መሆናቸው ቢያስደስትም ራሱን የቻለ ጥቅምና ጉዳት(ስጋት) ያለበት መሆኑ ግን ግልፅ ነው። (አንድ ታዛቢ እንዳለው አይበለውና ባንዱ ግንባር ችግር ቢፈጠር በዛ ሰዓት ወታደር ሊያሰማሩ ነው ወይስ ማሽን ሊያስነሱ... )የሆነው ሆኖ ለጊዜው ግን METEC ቢቻል በተመረጡ ዘርፎች ላይ ብቻ ቢሰማራ፣ ዓለም አቀፍ ተፎካካሪ ሁኑ እየተባሉ የሚሰበኩትንና እደጉ (አደጋችሁ?) ተብለው የሚሸለሙትን ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉትንና አዲስ መጭዎችንም የግል ፋብሪካዎች ባያቀጭጭ መልካም ነው። የራሱን ሚናና ሜዳ ይምረጥ፣ ለሌሎቹም ሜዳቸውን ይተውላቸው። ካልሆነ ግን የግሉ ዘርፍ እንኩዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ አገር አቀፍም ነዋሪ መሆን አይችሉም.... እኛም ተከፍተው ተዘጉ እንዳንል፣ ፖሊሲዉም እርስ በርሱ እንዳይጣረስ ቢታሰብበት መልካም ነው ።

Wednesday, December 12, 2012

የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች (ክፍል ፪)



የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች (የቀጠለ)

ለኢንዱስትሪዎቻችን ያልተጠና “ኩረጃን”ና የተናጠል ጉዞ ባህልን በማስወገድ መቀናጀትና በአቅርቦት ሰንሰለት  መመጋገብ አስፈላጊና አዋጭ መሆኑ ያጠራጥርም፡፡ ለምሳሌ፡- ሸሚዝ የሚያመርት ፋብሪካ  ለምርት ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የሚያቀርብለትን አቅራቢ /አምራች/ ይፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚታየው ባህል ግን ቀድሞ ከነበረው የሸሚዝ ፋብሪካ ጎረቤት ሌላ የሸሚዝ ፋብሪካ መክፈት ቢሆንም የተሻለው አማራጭ ግን በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ክፍተት ባለበት ቦታ ተሰማርቶ ውጤታማ  መሆን ነው፡፡(ለምሳሌ፡- ለፋብሪካው ጥሬ እቃ ማቅረብ ወይም ከፋብሪካው ምርቱን ተቀብሎ እሴት ጨምሮ ለተጠቃሚ ማቅረብ፤ ካልሆነም ሌላ ከሸሚዝ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የስራ መስክ ላይ መሰማራት ሊሆን ይችላል፡፡) ይህን መሰሉን የአቅርቦት ሰንሰለትን መመጋገብንና ጥምረትን መሠረት በማድረግ መሰማራት ሁሉንም አካላት የበለጠ ትርፋማ ያደርጋል፡፡  ካልሆነ በአንድ ዓይነት የአቅርቦት ሰንሰለት ምድብ ላይ መሰባሰብና ውስን የሆነን ደንበኛ መሻማት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለት ሁነትም የሚያሳየው  ይህንኑ ነው፡፡ ሁሉም አቅራቢ ከሆነ ማን ያመርታል?  ሁሉም አምራች ከሆነ ማን ያቀርባል? ከምርት ቦታ አጓጉዞ ከሽያጭ ቦታ የሚያደርስና የሚያከፋፍል/የሚሸጥ ከሌለ ለምንስ ይመረታል? የእነዚህ የሁሉም  የሰንሰለቱ ኣባላት  የተቀናጀ ተሳትፎ የመጨረሻውን ተጠቃሚ ደንበ,ኛ ለማርካት አስፈላጊ ነው፡፡ በመቀናጀት የተሟላና የተመረጠ አገልግሎት በመስጠት ደንበኛን ለማርካት ይቻላል፡፡  ጫማ የሚገዛ ተጠቃሚ ካልሲ እንደሚያስፈልገው ይታወቃል፡፡ ሁሉም ጫማ ብቻ አምራችና አቅራቢ ቢሆን ካልሲ አቅራቢ /አምራች/ ባይኖር የመጨረሻው ተጠቃሚ ደንበኛ ሙሉ እርካታ ላያገኝ ይችላል፤ በጫማው ምርት ስራ የተሰማሩ ብዙዎች ከሆኑ ሌሎች ደግሞ ለደንበኛው ተጨማሪ የሚያስፈልጉት ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ማተኮር ሊያዋጣቸው ይችላል፡፡ ይህ ሲባል ጫማ አምራች (አቅራቢ/ ስላለ ሌላ በዚህ መስክ ፈጽሞ አይሠማራ ማለት አይደለም፤ የተሻለ ምርት አቅርቦ ተወዳዳሪ (ተመራጭ) መሆን የሚችል አካል ቢሰማራ ያወጣው ይሆናልና፡፡ (ካልሆነ በየሰፈሩ በተመሳሳይ መስክና ጊዜ ተከፍተው በዓመቱ እንደተዘጉት ብዙ “ኮሌጆቻችን” አይነት እጣ ነው ትርፉ፡፡)

ሌላው የአቅርቦት ሰንሰለትን ቅድመ ጥምረትም ሆነ ድኅረ ጥምረት ዉጤታማ ከሚያደርጉት ዋና ግብዓቶች መካከል የሰው ኃይል/ሃብት ዋናዉን ድርሻ ይይዛል፡፡ በኢንዳስትሪዎቻችን በተለይም በፋብሪካዎቻችን ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል ስናይ በአብዛኛው በ”መደበኛ”ና አስፈላጊ የትምህርት መስክና ስልጠና ውስጥ ያላለፈ መሆኑ የአቅርቦት ሰንሰለቱን አስተዳደር  ብቻ ሳይሆን የ “ውስጥ” ጥንካሬንና ተፎካካሪነትንም ለማምጣት የአቅም ችግር እንዲኖርበት አድርጎታል፡፡ በትምህርት አቅርቦቱና አሰጣጡ ዙሪያ ,ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳለ ሆኖ ከየትምህርት መስኩ የሚመረቀውም አማራጭ ከማጣት አንጻር እንጂ በተለይ በፋብሪካ ውስጥ ገብቶ ለመስራት ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነት አጠያያቂ ነው፡፡ ተገቢውን የሰው ኃይል በተገቢው ቦታ ማሰማራት ላይ ያለውም ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ በማኅበረሰባችን ዘንድም በተለይ በአንዳንድ አከባቢ ሰፋ ባለ መልኩ በኢንዱስትሪ/ በፋብሪካ/ ውስጥ መስራት እንደ ተወዳጅ የስራ ዘርፍ የሚመረጥ አይደለም፡፡ ከአለባበስ ጀምሮ የፋብሪካ የስራ ልብስን የለበሰ ሰው ሲታይ የሚሠጠው ግምት/”ክብር”/ አናሳ ነው፡፡ በተለምዶ በአንዳንድ ቦታ ሲነገር እንደሚሰማው አለባበሱ “አዳፋ” የሆነና የፋብሪካ የስራ ልብስን አይነት ልብስ ለብሶ ሲታይ “ዛሬስ የፋብሪካ ሰራተኛ መስለሃል/መስለሻል” የሚባለው የዚሁ የማኅበረሰባዊ አመለካከት ነጸብራቅ ነው፡፡  በፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ መሃንዲሶችንም  “መሃንዲስ” መሆናቸውንና  መሃንዲስ መባላቸውንም የማያውቅ የኅብረተሰብ ክፍል እጅግ ብዙ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

በመጨረሻም በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ወሳኝ የሚባለውና ለአቅርቦት ሰንሰለት ህልውና ምክንያት የሚሆነው የአቅርቦት ሰንሰለቱ ምርት/አገልግሎት/ ተጠቃሚ ደንበኛ ነው፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለት ዋና ዓላማም ተጠቃሚ ደንበኛን በማርካት በገበያ ላይ ተፎካካሪና ትርፋማ ሆኖ መቀጠል ነው፡፡ ስለዚህ ይህ በሰንሰለቱ “የመጨረሻ እርከን” ላይ የሚገኘው አካል በሰንሰለቱ አልፎ የሚመጣለትን ምርት ካልተጠቀመ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡  አንዳንድ ጥናቶችና የግል ምልከታዎች እንደሚያሳዩት በተጠቃሚው ማኅበረሰባችን ዘንድ የሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ምርቶችን (የሃገር በቀል ኢንዳስትሪ) ምርትን  ለመግዛት ያለው ፍላጎትም ሆነ ባህል ጎልቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሱ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም የምርት ጥራት ማነስንና የዋጋ መወደድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሁንና አብዛኛው ተጠቃሚ ለማለት በሚያስደፍርበት ሁኔታ የዋጋና የጥራትን ጉዳይ በትክክል ግምት ውስጥ ሳያስገባ ከ”ውጭ” የመጣን(የተመረተን) ምርት በብዛት ሲመር,ጥ ይታያል፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የተመረቱ  ሸሚዞች በላያቸው ላይ ያለውን  ጽሑፍና በሸሚዙ ላይ የሚያያዘውን “ታግ” በማቀያየር ለገበያና ለእይታ በዐዉደ ርዕይ ላይ ቀርበው ሸሚዞቹን በጣም በተለያየ ዋጋ ለመሸጥ ተችሏል፡፡ የሚገርመው ሁሉም ሸሚዞች እኩል ጥራት ያላቸው ሲሆኑ የተለያዩት ላያቸው ላይ ባለው ጸሑፍና ሸሚዞቹ ላይ በተያያዘው የተሰሩበትን ሃገር በሚገልጸው ታግ ብቻ ነበር ፡፤  ከፊሎቹ “በኢትዮጵያ የተመረተ” ና ሌሎቹ ደግሞ “በአሜሪካ የተመረተ” የሚል ታግ ያላቸው ሲሆኑ ሸሚዞቹ የሽያጭ ዋጋቸው በእጥፍ ተለያይቶ ቢቀርብም በዋጋም ከ”አትዮጵያኖቹ” ሸሚዞች  ከእጥፍ በላይ የሆኑት “አሜሪካኖቹ” ሸሚዞች በብዛት ተሸጠዋል፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃገር ምርትን የመጠቀም አዝማሚያ እየታየ መሆኑ የሚያበረታታና የሚበረታታ ጅምር ሲሆን በተለያዩ ዐዉደ ርእይ ዝግጅቶችና “የኢትዮጵያን ይግዙ” አይነት የቅስቀሳ ስራዎች የሃገራችንን ተጠቃሚ ወደ ሃገር በቀል ምርቶች እንዲያዘነብል የሚያግዙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ የሌሎች በማደግ ላይ ያሉና ያደጉ ሃገራት ኢንዱስትሪዎች  ልምድም የሚያሳየው ለኢንዱስትሪዎቹ ማደግ አካባቢያዊና ሃገራዊ  ተጠቃሚ ደንበኛ መብዛቱ ውስጣዊ አቅም ፈጥረው ኢንዱስትሪዎቹን አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዲሆን አስችሏዋቸዋል፡፡ [p.s. ስለዚህ ሁላችንንም በተናጠል በሚያሳትፈው “የመጨረሻው” የአቅርቦት ሰንሰለቱ ምድብ  ቢያንስ ድርሻችንን እንድንወጣ  ግድ ይለናል፡፡]

የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች (ክፍል ፩)


 የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች (ክፍል ፩)

የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና  ገና በማደግ ላይ ያለ የሙያ ዘርፍ ሲሆን ባደጉ አገሮች በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት እያገኘ ያለ የአስተዳደርና ምህንድስና ዘርፍ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ የሚለው ቃል ሰፊና የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ የሚታይና የሚዳሰስ ቁሳዊ ምርት የሚያመርቱትንና የማይታይና የማይዳሰስ አገልግሎት የሚሰጡትንም ጭምር ያካትታል፡፡ ሆኖም በጽሑፉ ውስጥ በአብዛኛው ትኩረት የሚሠጠው ለሚታይ ምርት አምራች ኢንዱስትሪው (በአብዛኛው “ፋብሪካ” ለሚባለው) ይሆናል፡፡ ይህ በተለይ በሃገራችን በብዙ መልኩ ችግሮች የሚታዩበትና ገና በማደግ ላይ ያለም ስለሆነ ትኩረት ተደርጎበታል፡፡

አብዛኞቹ የሃገራችን ኢንዳስትሪዎች ለአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርና ምህንድስና ብዙም ትኩረት ሲሰጡ አይታይም፡፡ የብዙዎቹ ኢንዳስትሪዎች ትኩረትም አምርተው በሚሸጡት ምርት ዓይነትና ብዛት እንዲሁም የውስጥ አቅምን ማሳደግ ላይ እንጅ በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ባላቸው ጥምረት (የቅንጅት ሥራ) ውጤት ላይ አይደለም፡፡አስቀድሞም በቅድመ ትግበራና የአዋጭነት ጥናት ወቅትም ቢሆን ለአቅርቦት ሰንሰለት ትኩረት ስለሚነፈገው አዲስ የሚከፈቱ ኢንዱስትሪዎች  ከየት ጥሬ ዕቃ እንደሚያገኙ፣ ከማን ጋር አብረው መስራትና እንዴት መስራት እንዳለባቸው ሳይጤን ዘለው ወደ የማምረቻ ፋብሪካ (የአገልግሎት መስጫ ተቋም) መክፈት መሄድ የሚታየው፡፡

በዚህ ዘመን እንደሚታየው ደግሞ የገበያ ፉክክሩ የአንድ አምራች/አቅራቢ/ ድርጅት ከሌላ ተመሳሳይ ምርት አምራች/አቅራቢ/ ድርጅት ጋር ሳይሆን የአንድ ምርት የአቅርቦት ሰንሰለት ከሌላ ተመሳሳይ የአቅርቦት ሰንሰለት ጋር ያለ ፉክክር ነው፡፡ በዚህ የፉክክር ገበያ ውስጥ አሸናፊ ለመሆን የአቅርቦት ሰንሰለትን መሰረት በማድረግ መቀናጀት ያስፈልጋል፡፡ የተናጠል ሩጫ የትም ስለማያደርስ በተለይም ገና ላላደጉ ኢንዳስትሪዎቻችን እርስ በርስ በመቀናጀትና በመመጋገብ መጓዝ ካልተቻለ አገር አቀፋዊ ሆነ አለም አቀፋዊ ብቁ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም፡፡ ውድድሩ  የአቅርቦት ሰንሰለት እንጅ የተናጠል  ውድድር አይደለምና፡፡የአቅርቦት ሰንሰለት ጥምረት ዋና ዓላማም የደንበኛን ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ በማርካት ከሌላው የአቅርቦት ሰንሰለት ልቆ በመገኘት በገበያ ላይ የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን ነው፡፡ጥምረቱ በመረጃ መቀናጀትንየእቅድ ጥምረትንና የአሠራር ሂደት ጥምረትን ያካትታል፡፡

በአብዛኛው የኢንዱስትሪዎቻችን የስራ ባህልም “የቀጥታ ግልበጣ” ን ወይም “የኩረጃን” ልምድ መሠረት ያደረገና ተመሳሳይ አሠራርን የተከተለ ነው፡፡ ይህም ማለት በአንዱ ፋብሪካ የታየው አሠራር ምንም ጥቅምና ጉዳትን የማገናዘብና የማስላት ስራ ሳይካሄድበት በተመሳሳይ ወቅትና ሁኔታ ተደጋግሞ ሲሰራበት ይታያል፡፡ ካደጉ አገሮችም ሆነ ከተፎካካሪ ሃገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ኮርጆ እሴት ጨምሮ መወዳደር ጤናማና አዋጭ ስለሆነ እንደርሱ አይነቱ ኩረጃ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ በአለም ላይ ያለውም ልምድ የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የቻይና ኢንዱስትሪዎችን ብንወስድ በአብዛኛው በመኮረጅበማላመድና በማሻሻል ላይ ያተኮረ ስልት ይከተላሉ፡፡ ኮርጀው ካገኙት ላይም እሴት በመጨመርና በማሻሻል የተሻለ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ነገር ግን በእኛ ሃገር ኢንዱስትሪዎች (ከትናንሽ እስከ ትላልቅ  ባሉ ኢንዱስትሪዎች) ዘንድ የሚታየው አዋጭነትንና አቅምን እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫን ሳያገናዝቡ ወደ ጭፍን ኩረጃ የሚሄዱና በመጨረሻም የማይሳካላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡

አንዱ ኢንዱስትሪ ከሌላው ጋር ተባብሮ የመስራት ባህልም የዳበረ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ዘርፍ በተለይ የለም ቢባል ይበልጥ ያስማማል፡፡  በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ በተመጋጋቢነትና በመቀናጀት ከመስራት ይልቅ በተናጠል መስራት የጎላ ባህላችን ነው፡፡ ይህ ባህል ይበልጥ ጎልቶ የሚንፀባረቀውም ከሀገራዊ/ከሃገር በቀል/ ኢንዳስትሪዎች ጋር አብሮ ከመስራት (ከመመጋገብ) ይልቅ ከሌሎች ኢንዳስትሪዎች ጋር “የማያዛልቅ”ና የማያዋጣ ጥምረት ሲፈጠር ይታያል፡፡ ማንም ኢንዱስትሪ ከሚፈልገው ጋር መተሳሰርና መመጋገብ የራሱ ምርጫ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በይበልጥ አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ካለው መሰል  ሃገራዊ/ሃገር በቀል/ ኢንዱስትሪ ጋር ተቀራርቦና ተመጋግቦ መስራቱ ይበልጥ ጠቃሚ ነው፡፡ የሃገሪቱም ኢንዳስትሪዎች  እርስ በርስ ተመጋግበው ያለመስራታቸው ጠንካራና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋልና፡፡
ይቀጥላል፡፡